በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዴት ይቋጭ ይሆን?



 

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት፣ አሁን ወደ አጓራባች ክልሎች አፋር እና አማራ ዘልቆ ከባድ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል።




በዚህ ጦርነት ሁሉም ተሳታፊ ወገኖች ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውድመት እንደፈጸሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለወራት ያደረጉት ምርመራ አመልክቷል።

የጦርነቱን መንስኤ በሚመለከት ሁሉም ወገኖች የየራሳቸውን ምክንያት የሚያቀርቡ ሲሆን አንዳቸው ሌላኛውን ወገን በጦርነት ቀስቃሽነት ይከሳሉ።

ጦርነቱ እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በምን ሁኔታ ይቋጭ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን እያሳሰበ ያለ ጉዳይ ነው።

አንዳንዶች የተራዘመ ጦርነት ሆኖ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብትና ሕዝብ ላይ ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል የሆናል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በአንደኛው ወገን የበላይነት የሚደመደም እንደሆነ ይጠቅሳሉ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተፋላሚዎቹ ወደ ድርድር ሄደው መፍትሔ ሊያገኙለት ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ጦርነቱ ያስከተለው ሞት እና መፈናቀል   

እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከተሞችን ተከትሎ የሚከናወን በመሆኑ የሚያስከትለው ጉዳትና መፈናቀል ቀላል የሚባል አይሆንም።

ለኤርትራ ነጻነት በተካሄደው ውግያ የተሳተፉት ኋላም በዐቃቢ ሕግነት እና በዳኝነት ያገለገገሉት አቶ ክፍለዮሐንስ ተወልደብርሃን ጦርነት በባህሪው አጥፊ መሆኑን በማንሳት "በተለይ በከተሞች የሚካሄደው ውጊያ በሰብአዊነት ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ብትሞክርም ከባድ መሳሪያ አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙ አደጋ ይደርሳል" ይላሉ።

ስለሆነም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኤርትራ ወታደሮች የህወሓት ታጣቂዎችን ለማደን ትግራይ ውስጥ በቆዩባቸው ሰባት ወራት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ዝርፊያዎች መፈጸማቸውን ይጠቅሳሉ።

ህወሓትም በማይካድራ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ንፁሃን ዜጎችን እንደገደለ የተባበሩት መንግሥታት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያካሄዱት ጥናት ገልጿል።

ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በመስፋፋቱ አካባቢዎቹን የተቆጣጠሩት የህወሓት አማጺያን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው የሚል ክስ እየቀረበባቸው ነው።

በተደጋጋሚ በንፁሃን ላይ ጥቃት እንደማያደርስ የሚገልጸው ህወሓት በበኩሉ ውንጀላዎቹ በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ይጠይቃል።

ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ተቀናቃኝ ኃይሎችም እርዳታ የሚቀርብበት መንገድን እንዲከፍቱ ጥሪ ሲቀርብ ቆይቷል።

በትግራይ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ከጦርነቱ በፊት 1.6 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ከሴፍትኔት በሚያገኙት እርዳታ ይኖሩ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የባንክ፣ የመብራት እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው የመንግሥት ሠራተኞች ሠራተኞችን ጨምሮ በክልሉ ኑሮ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አብዱራሕማን ሰይድ አቡሃሺም ያስረዳሉ።

በዚህ ምክንያት የህወሓት አማጺያን ትግራይ ላይ ያለው እገዳ እስኪነሳ እና ቀደም ሲል ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎችን መንግሥት እስኪቀበል ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ።

"ሙሉ ሰላም ሳይመጣ እንዲሁም ከአስተማማኝ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መንግሥት እገዳውን ይከፍተዋል የሚል ግምት የለኝም" የሚሉት አቶ አብዱራሕማን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት ስለሚያስፈልገው ሁኔታው በዚህ መንገድ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ አይችልም ሲሉ ያክላሉ።

አቶ ክፍለዮሐንስ በበኩላቸው ጦርነቱ ከዚህ በላይ ከተራዘመ የትግራይ ሕዝብ ሊከብደው እንደሚችል በመጥቀስ፣ የዓለም ማኅበረሰብ እርዳታ የሚያገኝበት መንገድ ለማመቻቸት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ብሏል።




አስተያየት ይለጥፉ

አዲስ የድሮ

Blog ads

Betseb media